Searching...
Oct 31, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ መግለጫም በማውጣት ተጠናቀቀ


  • ምልአተ ጉባኤው የዕርቀ ሰላሙን አምስት የመነጋገሪያ ነጥቦች ለይቷል፤
  • ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ደቡብ እና ምዕራብ አዲስ አበባን፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ሰሜንና ምሥራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከትን ይመራሉ፤
  • “የመነኰሳት መተዳደሪያ ደንብ” ይወጣል፤ የገዳማት ተወካዮች በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉና ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይደረጋል፤
  • ለአኵስም ጽዮን ማርያም አዲስ ንቡረእድ ይሾማል፤
  • ለካህናት ማሠልጠኛ፣ ለገዳማት፣ ለአብነት ት/ቤቶች (ብር 10 ሚልዮን+) እና ለሌሎችም የልማት ዕቅዶች ማስፈጸሚያ ከብር 128 ሚልዮን በላይ በጀት ተመድቧል፤

(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 21/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶ. 31/2012)፦ ላለፉት ዐሥር ቀናት በሥራ ላይ የቆየው የጥቅምት 2005 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ፣ ጥቅምት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ላይ መግለጫ ተጠናቀቀ፡፡ በ“ልዩ ልዩ ጉዳዮች” አጀንዳዎች ሥር በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰውና የበጀት ምደባን ጨምሮ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቀደም ሲል ውሳኔ ያሳለፈባቸውን የመነጋገሪያ ነጥቦች ዳግመኛ በጥልቀት ሲመለከት የቆየው ምልአተ ጉባኤው÷ ከኅዳር 26 - 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ ለሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ውይይት የቅዱስ ሲኖዶሱ ልኡክ መነጋገሪያ (መደራደሪያ?) የሚያደርጋቸውን አምስት ነጥቦች መለየቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱን አቋም የሚገልጡ ናቸው የተባሉት አምስቱ ነጥቦች “የሰላምና አንድነት ጉባኤው” ላቀረባቸው ሰባት ጥያቄዎች በተሰጡ መልሶች ላይ በመመሥረት የተዘጋጁ መኾናቸውን የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች አስረድተዋል፡፡


አምስቱን የልኡኩን የመነጋገሪያ ነጥቦች በዝርዝር ከመናገር የተቆጠቡት ምንጮቹ ከሰባቱ “የሰላምና አንድነት ጉባኤው”  ጥያቄዎች መካከል “ብሔራዊ ዕርቅ”ን አስመልክቶ የቀረበው “ከዕርቀ ሰላሙ አጀንዳ ጋራ ግንኙነት የለውም” በሚል ተቀባይነት እንዳላገኘ ጠቁመዋል፡፡ የአራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን የወደፊት ኹኔታ በተመለከተ ቀድሞም ከቅዱስነታቸው በተገለጸው መሠረት በመረጡት ስፍራ በጸሎት ተወስነው ሲኖሩ መንበረ ፓትርያርኩ ደግሞ ደመወዝ፣ መኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪና ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮች ያሟላል፤ የደኅንነት ጥበቃም ያደርግላቸዋል፡፡ በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የተሾሙ 49 ጳጳሳት በስደት በሚገኙት አባቶች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ፣ በአንጻሩም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በስደት የተሾሙት 13 ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶሱ ዘንድ ዕውቅናና ተቀባይነት እንዲያገኙ ምልአተ ጉባኤው አቋሙን ማስቀመጡ ተነግሯል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ “በጸሎት ተወስነው በመረጡት ስፍራ ይኑሩ” ሲባል በሕገ ቤተ ክርስቲያን ለፓትርያርኩ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት÷ በመንበረ ፓትርያርኩ እየተገኙ የቅዱስ ሲኖዶሱን ስብሰባ በርእሰ መንበርነት መምራትና ውሳኔዎቹን ማስፈጸምን፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ኤጲስ ቆጶሳትን፣ የታላላቅ አድባራትና ገዳማት አለቆችንና አበምኔቶች መሾምን፤ በውጭ ግንኙነት ቤተ ክርስቲያንን መወከልን. . . ወዘተ እንደማያካትት ግልጽ ነው ያሉት ምንጮቹ መንበሩን በተመለከተ የሚታየው የምልአተ ጉባኤ አዝማሚያ የቅዱስነታቸውን ፈቃድ በሚያጤን (ባካተተ) አካሄድ ወደ ስድስተኛው ፓትርያርክ ሹመት መቀጠል መኾኑን አልሸሸጉም፡፡

ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ የሚሟገቱና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሕይወት እስካሉ ድረስ መንበረ ተክለ ሃይማኖት በእንደራሴ ወይም በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚሹ ወገኖች ግን በስድስተኛው ፓትርያርክ ሹመት ጉዳይ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳስባሉ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ከመኾናቸው በፊት የመጨረሻው ግብጻዊ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ እስኪያርፉ ድረስ በዐቃቤ መንበርነት የቆዩባቸውን ሦስት ዓመታት (ሐምሌ 1940 - ጥቅምት 1943 ዓ.ም)፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በቀድሞው መንግሥት በእስር ላይ ሳሉ ሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እስኪሾሙ ድረስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዐቃቤ መንበር የነበሩበትን አንድ ዓመት፣ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በተደረገባቸው ጫና ከመንበራቸው ወርደው መጀመሪያ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በኋላም ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የነበሩበትን ዐሥራ አንድ ወራት በማስታወስም በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የመቆየት ተሞክሮ በመጥቀስ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲባል ትዕግሥት ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተደራጀውና የጳጳሳትን ዝውውር የሚመለከተው ኮሚቴ ለምልአተ ጉባኤው ባቀረበው ሪፖርት በሕመምና ተጓዳኝ ምክንያቶች የዝውውር ጥያቄ ያቀረቡ ብፁዓን አባቶችን ጉዳይ ተመልክቷል፡፡ ለመልካም አስተዳደር መስፈን ሲባል በጥናት ከቀረቡት በርካታ አማራጮች መካከል በአራት አህጉረ ስብከት የተከፈለው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እስከ መጪው ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ድረስ በሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እየተመሩ ጽ/ቤቶቻቸውንና አስተዳደራቸውን ሲያጠናክሩ እንዲቆዩ ወስኗል፡፡

በዚህም መሠረት ቀደም ሲል ሀገረ ስብከቱን ከሰሜን ሸዋ - ሰላሌ ሀ/ስብከት ጋራ ደርበው ሲመሩ የቆዩት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ተነሥተው በአዲሱ አደረጃጀት መሠረት የምዕራብ ሐረርጌ (አሰበ ተፈሪ) ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜንና ምሥራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከትን፣ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ዞን ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሀ/ስብከታቸውን እንደያዙ የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባን እንዲመሩ ተወስኗል፡፡ አመራሩ ለሁለቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተሰጠው ዕጣ የዝውውር ጥያቄ ካቀረቡት አራት ብፁዓን አባቶች (ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል) መካከል በተደረገው/በተጣለው ዕጣ መኾኑ ተዘግቧል፡፡ የአህጉረ ስብከቱ አድባራትና ገዳማት አቤቱታ የቀረበባቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጉዳይም በዚሁ አዲስ አደረጃጀት ሂደት መፍትሔ እንደሚሰጠው እየተጠበቀ ነው፡፡

በገዳማት ጉዳይ አስቀድሞ ያደረገውን ውይይትና ያስተላለፈውን ውሳኔ በትናንትናው ውሎው ዳግመኛ በማንሣት በጥልቀት የተወያየው ምልአተ ጉባኤው በ31ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ባስተላለፈው ውሳኔና የአቋም መግለጫ መሠረት የገዳማት ተወካዮች የዓመታዊው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተሳታፊዎች እንዲኾኑ ወስኗል፡፡ በመኾኑም ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የገዳማት አበምኔቶች በዓለም አቀፉና አገር ዓቀፉ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ላይ እየተገኙ ሥርዐተ ምንኵስናውን (የገዳማቱን የአንድነት ኑሮ)፣ መንፈሳዊ አገልግሎቶችና የልማት ክንውን የተመለከቱ ሪፖርቶችን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በምንኵስና ሕይወት ከሚታየው ችግር አኳያ መነኰሳቱን መሰል መነኰሳት እና እውነተኛ መነኰሳት በሚል ከፍሎ ችግሩን በጥልቀት የዳሰሰው ምልአተ ጉባኤው÷ የሌላ እምነት (የእስልምና ወይም የፕሮቴስታንት) ተከታይ ኾነው ሳለ በምናኔ ስም ወደ ገዳሞቻችን ሰርገው ገብተው የጥፋትና ቅሰጣ ተልእኮ በመፈጸም ላይ የሚገኙ፤ የእኛኑ ቆብ ደፍተው የቤተ ክርስቲያኒቱን ገጽታ በሚያበላሹና ሥርዐተ ምንኵስናን በሚያስንቁ/በሚያስነቅፉ አስነዋሪ ተግባራት ላይ የመሰማራት ዓላማ ያላቸው፤ የገዳምም የቀበሌ ነዋሪነትም መታወቂያ ይዘው እንዳመቺነቱ የሚያጭበርብሩ፤ የመንፈሳዊ ኮሌጆች ወይም የካህናት ማሠልጠኛዎች ምሩቃን ሳይሆኑ ነን በሚል የሐሰት ማኅተሞችን ይዘው የሐሰት ሰነዶችን አስመስለው በማዘጋጀት የተካኑ፤ የአክሊለ ሦኩ ምሳሌ የኾነውን ቆብዕ ዘሠለስቱ ደቂቅ፣ የሐብለ ተቀስፎ ቅናት ዘዮሐንስ መጥምቅ እንደሚገባቸው ሳይሆን እንዳሻቸው የሚለብሱ፤ “ሥራ እናስቀጥራችኋለን፤ ውጭ አገር እንልካችኋለን. . .” በሚል ባለትዳር ወይዛዝርትን ሳይቀር የሚያነውሩ፣ ከትዳር የሚያፋቱና ሀብታቸውን የሚመዘብሩ. . . እንዳሉ ጉባኤው በማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ ከሚገኙት መነኰሳት ጭምር በምርመራ ከተገኘው መረጃ ለይቷል፡፡ አህጉረ ስብከት፣ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ እና ምእመናን በአጠቃላይ ከመንግሥት አካላት ጋራ በመተባበር በእኒህ መሰል መነኰሳት ላይ በቀጣይ ለሚወሰደው ርምጃ እንዲተባበሩም በይፋ ጥሪ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

እውነተኞች መነኰሳት በሚል የተለዩትን በተመለከተ ከየት እንደመጡ፣ በትክክለኛው የአመክሮ ጊዜ (ሦስት ዓመት) እና ተገቢውን ትምህርት ወስደው መመንኰሳቸው ይጣራል፡፡ ይህም ገዳማት ለአህጉረ ስብከትና በየደረጃው ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት በሚያቀርቡት የእያንዳንዱ መነኮስ ማኅደር (ፕሮፋይል) ሪፖርት እንዲጣራና እንዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡ መነኰሳት ከገዳማቸው ያለ ምክንያት እንዳይወጡና የሚወጡም ከኾነ ስለሚወጡበት ምክንያት የገዳሙ አስተዳደር ለሀ/ስብከት ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ይደረጋል፡፡

ምልአተ ጉባኤው በየአህጉረ ስብከቱ እንዲፈጸሙ ያጸደቃቸውን የመንፈሳዊ አገልግሎትና ዝርዝር የልማት ተግባራት ዕቅዶች መከናወን በበጀት ለመደገፍ ባደረገው የምደባ ውይይት ከብር 128 ሚልዮን ብር በላይ ገንዘብ ለገዳማት፣ ለአብነት ት/ቤቶች፣ ለካህናት ማሠልጠኛዎች፣ ለምዕራብ ወለጋ ሁለገብ ሕንጻ (በኦሮምኛ ቋንቋ የካህናት ሥልጠና የሚሰጥበትን ተቋም ወደ ኮሌጅ ለማሳደግ ታቅዷል)፣ ለአኵስም ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሕንጻ ማስጨረሻና ለመሳሰሉት ሥራዎች እንዲውል ወስኗል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
የቅ/ሲኖዶስን ውሳኔዎች ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ይመልከ

 
31,October 2012
Deje selam.

0 comments :

Post a Comment